አገልግሎቱ የፈቃድ ስረዛው የተላለፈው በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በተሰጡ መመሪያዎች እና በሕግ በተሰጠው የቁጥጥር ስልጣን መሰረት መሆኑን ገልጿል። ይህ ውሳኔ በዘርፉ ላይ በተካሄደ አገር አቀፍ ጥልቅ ግምገማ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ "በሥራ ላይ ባሉትና ቀደም ሲል በይፋ በታገዱት በሁሉም የውርርድ ድርጅቶች በእኩልነት ተፈጻሚ ይሆናል" ተብሏል።
Table of contents [Show]
የውሳኔው ዋነኛ ምክንያቶች
የሎተሪ አገልግሎት የፈቃድ ስረዛ ውሳኔው የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር የተወሰደ እርምጃ ነው ሲል የጠቆመ ሲሆን፣ በዘርፉ ውስጥ የተንሰራፋውን ህገ-ወጥ አሰራር በዝርዝር አስቀምጧል። በመግለጫው መሰረት፣ ውሳኔውን ያስከተሉት ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦
- የተንሰራፋ ሕገ-ወጥ አሰራርና የውል ጥሰት፡ በሂደት ላይ ያለው ምርመራ በውርርድ ዘርፉ ውስጥ ሰፊ የሆነ ሕገ-ወጥ አሰራር እና የፈቃድ ውል ጥሰት መኖሩን በግልጽ አመላክቷል።
- ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የሆኑ የገንዘብ ዝውውሮች፡ በዘርፉ በኩል ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውሮች (Illicit Financial Flows) መኖራቸው ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የሚሆኑ አሰራሮች እንደተፈጠሩ ምርመራው አረጋግጧል።
- የሕዝብ ጥቅም ጥበቃ: ውሳኔው በዋናነት ሕዝብን ከማኅበራዊ ቀውሶች እና ከፋይናንስ ስጋቶች ለመጠበቅ ያለመ ነው።
ለስፖርት ውርርድ ድርጅቶች የተሰጡ ጥብቅ መመሪያዎች
የሥራ ፈቃዱ መሰረዙን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት የውርርድ ድርጅቶች ወዲያውኑ ሊተገብሯቸው የሚገቡ አራት ዋና ዋና መመሪያዎችን አስተላልፏል።
| ተግባር | መመሪያው |
|---|---|
| የሥራ ማቆም | ከታኅሳስ 06 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአካልም ሆነ በዲጂታል ወይም በሌላ መንገድ የሚካሄድ ማንኛውንም የውርርድ ሥራ ወዲያውኑ ማቋረጥ። |
| የገንዘብ ዝውውር | ሁሉም የገንዘብ ማስገቢያ መንገዶች (Deposit Gateways) አገልግሎት መስጠት ማቆም አለባቸው። አዲስ ውርርድ መቀበል ፈጽሞ አይቻልም። |
| የመረጃ ጥበቃ | ሁሉም የሰርቨር መረጃዎችን፣ የፋይናንስ መዝገቦችን እና የተጠቃሚ መረጃዎችን በጥብቅ ጠብቀው የማቆየት ግዴታ አለባቸው። |
| የሕግ ተጠያቂነት | ማስረጃን ማጥፋት፣ መቀየር ወይም ማሸሽ በወንጀል ሕጉ መሰረት የሚያስቀጣ በመሆኑ በጥብቅ የተከለከለ ነው። |
ለፋይናንስ ተቋማት የተላለፈው ትዕዛዝ
አገልግሎቱ ለፋይናንስ ተቋማት (ባንኮች፣ የፔይመንት ኢንስቱርመንት ኢሹወርስ እና የፔይመንት ሲስተም ኦፕሬተሮች) የተለየ እና ጥብቅ መመሪያ አስተላልፏል።
- የሽያጭ እንቅስቃሴ መከልከል: ከታኅሳስ 06 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ፣ የሁሉም የውርርድ ድርጅቶች የሥራ ፈቃድ በመሰረዙ፣ በፋይናንስ ተቋማቱ በኩል የውርርድ ድርጅቶቹ ማንኛውንም የሽያጭ እንቅስቃሴ እንዳያከናውኑ ጥብቅ መመሪያ ተሰጥቷል።
የክትትልና የሕግ ተጠያቂነት ማስጠንቀቂያ
የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት እንደ ተቆጣጣሪና አስፈጻሚ አካል በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት፣ ይህን ውሳኔ ከሁሉም መንግስት ተቋማት ጋር በመተባበር በጥብቅ እንደሚከታተልና መመሪያውን የሚጥስ ማንኛውም አካል በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን አስጠንቅቋል።